የተጎዳንና የሚያሳክክ የሰውነት ቆዳን እንዴት ማከም እንችላለን ?
የቆዳ ማሳከክ የልዩ ልዩ የቆዳ ችግሮች ማሳያ ወይም ጠንከር ያሉ የውስጣዊ አካል ሕመሞች እና የተዛማጅ ችግሮች ምልክት ሊኾን ይችላል፡፡ የአለርጂ እና የነፍሳት ንክሻም የቆዳ ማሳከክን ሊፈጥር ይችላል፡፡
አንዴ የችግሩን መንስኤ ከተረዳን ከነዚህ በተፈጥሮ ከሚዘጋጁ መድኃኒቶች አንዱን መጠቀም እና ለሚያሳክከን የቆዳችን ክፍል መፍትሔ ማበጀት እንችላለን፡፡
- ቀዝቃዛ ነገሮች
- የአጃ እህል
- ካሞማይል
- ሬት
ቀዝቃዛ ወይም እርጥብ ጨርቅ ወይም በጨርቅ አልያም በላስቲክ የተጠቀለለ በረዶ ብዙ ጊዜ ለሚቆጠቁጥ ወይም ለሚያሳክክ ቆዳ እፎይታን ይሰጣሉ፡፡ በቀዝቃዛ ውኃ የራሰውን ጨርቅ በተጎዳው የሰውነታችን ክፍል ላይ ከአምስት እስከ አሥር ለሚደርሱ ደቂቃዎች ማስቀመጥ! ቅዝቃዜው የመቆጥቆጡንና የማሳከኩን ስሜት በፍጥነት ያስታግስልናል፡፡
ብዙ ሰዎች የአጃ ዱቄትን ለሚቆጠቁጥና ለሚያሳክክ ቆዳ ሕመም ማስታገሻነት ሲጠቀሙት ይስተዋላል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አጃ በውስጡ የማሳከክ እና የመቆጥቆጥ ስሜትን የሚያስወግድ ንጥረ ነገር በመያዙ ነው፡፡ እርስዎም ይህ የማቃጠልና የመቆጥቆጥ ስሜት በተሰማዎት ጊዜ አንድ ሲኒ የአጃ ዱቄት በጨርቅ በመጠቅለልና ጥቅሉን በሙቅ ውኃ ውስጥ በማስቀመጥ መድኃኒት ማበጀት ይቻላል፡፡
ይህ ባለ ውብ አበባ እፅዋት ብዙውን ጊዜ ለሻይ እና ውብ የሰውነት ቆዳን ለመጎናፀፍ ሲባል አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡ የካሞማይልን ሻይ ሰውነት ላይ በድርቀትም ኾነ በአለርጂ ምክንያት የሚከሰትን የማቃጠልና የመቆጥቆጥ ስሜት ለማስታገስ መጠቀም እንችላለን፡፡ ካሞማይል ከዚኽ ጥቅሙ ባሻገር ለክሬም እና ቅባት እንዲኹም ለልዩ ልዩ የመድኃኒት ምርቶች በግብአትነት የሚውል እጅግ አስፈላጊ ንጥረ ነገር ያለው አበባማ ተክል ነው፡፡
የሬት ተክል የሚያሳክክ የቆዳ በሽታን ጨምሮ ለብዙ የቆዳ ላይ ችግሮች ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ የመቆጥቆጥ እና የማቃጠል ስሜቶችን ከማስታገሱ ባሻገር የማቃጠል እና የቆዳ መሰነጣጠቅ ችግሮችን ያስወግዳል፡፡ የሬት ተክልን ፈሳሽ ጥቅም ላይ ከማዋልዎ በፊት ቅጠሉን ለተወሰነ ሰዓት በማቀዝቀዣ ውስጥ ያስቀምጡት፡፡ ይህን ማድረግዎ የቅጠሉን የፈሳሽ መጠን ለመጨመር በሚገባ ይረዳዎታል፡፡ ካልኾነም እንደ ቫዝሊን ሎሽን ያሉ ማለስለሻዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ ከቁስል ጋር ንክኪ እንዳይፈጥር መጠንቀቅዎን አይርሱ!
አንዳንዶች እርሾን ለሚያቃጥልና ለሚቆጠቁጥ የሰውነት ቆዳ መጠቀም መድኃኒት እንደኾነ ያስባሉ፡፡ ግን ፍቱን መድኃኒት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስናቸው መፍትሔዎች ሊሠሩ ካልቻሉ እና ችግሮቹ ከቀጠሉ ሐኪም ማማከር ይጠበቅብዎታል፡፡ በዚኽም ሐኪምዎ ክሬሞችን እና ቅባቶችን ሊያዙልዎት ይችላሉ፡፡
የሰውነታችንን ቆዳ የሚቆጠቁጠውና የሚያቃጥለው ስሜት ተመልሶ እንዳይመጣ እንዴት መከላከል እንችላለን?
ያለፈው የማቃጠል እና የመቆጥቆጥ ስሜት በድጋሚ እንዳይመለስ ማድረግ የሚገባን ቀዳሚው ነገር ችግሩን በድጋሚ ከሚቀሰቅሱት ነገሮች በተቻለ መጠን መራቅ ነው፡፡ ይህ የማሳከክ ስሜት እንዳይመለስ ቆዳችንን መንከባከብ ስለምንችልባቸው መንገዶች እንጠቁምዎ!
- የሚቆጠቁጥና የሚያሳክክ የሰውነት ቆዳ ብዙውን ጊዜ ለድርቀት የተጋለጠ ነው፡፡ ይኽንን ደግሞ በየቀኑ እንደቫዝሊን ሎሽን ያሉ ማለስለሻዎችን በመጠቀም ማስወገድ ይቻላል፡፡
- በሙቅ ውኃ ውስጥ ለረዥም ሰዓት የመቆየትን ወይም ሰፊ ሰዓት ወስዶ በሙቅ ውኃ የመታጠብን ልምድ መተው አለብዎት፡፡ ምክንያቱም ሙቅ ውኃ ሰውነታችን ላይ በበዛ ቁጥር ተፈጥሯዊ የሰውነታችንን ቅባቶች ሙልጭ አድርጎ በማስወገድ እና በማድረቅ የማሳከክ ስሜቱን ሊያበረታብን ይችላል፡፡
- ጠንካራ ወይም ከባድ ሽታ የሌላቸውን ሎሽኖችን እንዲኹም የገላ እና የልብስ ሳሙናዎችን ይጠቀሙ፡፡ መልካሙ መንገድ ከተፈጥሮ ንጥረ ነገሮች የተዘጋጁ እና ለሰውነትዎ የሚስማሙ የገላ እና የልብስ ሳሙናዎችን መጠቀም ወይም በቤት ውስጥ ማዘጋጀት ነው፡፡
- ምቾት የሚነሱ እና የሚኮሰኩሱ፣ የሚያሳክኩ ወይም ሰውነት ላይ ጥብቅ የሚሉ ልብሶችን ከመልበስ ይቆጠቡ፡፡ ከጥጥ የሚሠሩ ወይም ለስስላሳ ስሜትን የሚሰጡ እና በመጠኑ ለቀቅ ያሉ ልብሶችን በመልበስ የሰውነትዎ ቆዳ ሳይጨነቅ አየር እንዲያስወጣና እንዲያስገባ ይፍቀዱለት፡፡
ለሚያሳክክና ለሚያቃጥል ቆዳ በቤት ውስጥ ከሚገኙ ተፈጥሯዊ ግብአቶች የሚዘጋጁ ንጥረ ነገሮች እፎይታን በመስጠት እና ድርቀትን በመከላከል የሰውነታችን ቆዳ ራሱን እንዲጠግን ዕድል ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን መቆጥቆጡ እና ማቃጠሉ ያለምንም ለውጥ ከኹለት ሳምንታት በላይ ከዘለቀ ቀላል ያልኾነን ችግር እየጠቆመዎት ነው ማለት ነው፡፡
የማሳከኩ እና የመቆጥቆጡ ስሜት በመላው ሰውነትዎ ላይ ከተሰራጨ እንዲኹም ትኩሳት እና የክብደት መቀነስን በራስዎ ላይ ካስተዋሉ በፍጥነት ሐኪምዎን ያማክሩ!
በቅርብ ጊዜ የተሰጡ አስተያየቶች
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by libe
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by alemugetahun
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by Risky
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by belay
06 Jan 2015 @ 12:35 pm by መቅደላዊት ታከለ