ታዋቂዎቹን የፊት ማከሚያ “ማስኮች”ን እናስተዋውቆና መቼ እና እንዴት መጠቀም እንዳለብዎ ትንሽ እናካፍልዎ!
እንደቆዳዎ ዓይነት እና ኹኔታ ለልዩ ልዩ የሰውነት ቆዳ የሚስማሙ የፊት ማስኮች አሉ፡፡ እንደብዛታቸው አገልግሎታቸውም የተለያየ ነው፡፡ ለፊትዎ የሚጠቀሙት ማስክ ሥሪቱ ከልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ ነገሮች ልጣጭ ወይም ከውስጠኛው ክፍላቸው አልያም ለቆዳ እጅግ ተስማሚ ከኾኑ ውህዶች ድብልቅ የተዘጋጀ ሊኾን ይችላል፡፡ ኹሉም ግን የፊትዎን ቆዳ ልስላሴና አንጸባራቂነት ጠብቀው ውበትን ለማጎናጸፍ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡
አኹን የፊት ማስክን አጠቃቀምን በተመለከተ ሊያከናውኗቸው ስለሚገባዎት ነገሮችና በጭራሽ መሞከር ስለሌለብዎት ጉዳዮች አንዳንድ ምክሮችን እናካፍልዎታለን፡፡ .
1. ብጉርን ለማስወገድ የሚጠቀሟቸው የፊት ማስኮች
ብጉር በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሰውነታችንን ክፍሎች በተለይም ፊታችንን ደጋግሞ ሊጎበኝ የሚችል ነገር ነው፡፡ ይኽ የቆዳ ችግር ዘይት/ቅባት እንዲኹም የሞቱ የቆዳ ሴሎች የቆዳ ቀዳዳዎችን በሚደፍኑበት ጊዜ የሚፈጠር ነው፡፡ ለብጉር ማጥፊያ የሚኾን የፊት ማስክ በሚመርጡበት ወቅት ፊት ላይ ከተቀቡ በኋላ ልጠን የምናነሣቸውን የማስክ ዓይነቶች ላለመጠቀም ይጠንቀቁ፡፡ ምክንያቱም ቆዳዎትን በከፍተኛ ኹኔታ ሊጎዱት ይችላሉና!
2. ፊት ላይ ለሚወጣ ሽፍታ የሚኾን የፊት ማስክ
ሽፍታ በሰውነታችን ቆዳ ላይ የሚከሰተው በቆዳችን ውስጥ ያሉ የዘይት ዕጢዎች ብግነት ወይም ቁስለት በሚያጋጥማቸው ወቅት ነው፡፡ ሽፍታን ለመከላከል ከቤንቶናይት ወይም ከሰልፈር ውህድ በሚዘጋጅ የፊት ማስክ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ የዚኽን ውህድ ውጤታማነት ብዙዎች መስክረዋል፡፡ እርስዎም በሽፍታ ከተቸገሩ ይሞክሩት እና ጥራት ያለው የፊት ቆዳ ባለቤት ይኹኑ!
3. ለደረቅ ቆዳ የሚኾን የፊት ማስክ
ደረቅ የሰውነት ቆዳ ምንጊዜም የተጠማ ቆዳ ነው፡፡ ሰውነትዎ በቂ የኾነ እርጥበትን ማግኘት ካልቻለ ምቾትዎን በማጣት የሚጎረብጥ ስሜት ውስጥ ይገባሉ፡፡ በተለይ ገላዎትን ከታጠቡ በኋላ የሰውነትዎን እርጥበት እንዳያጡ ማለስለሻዎችን መጠቀም አለብዎት፡፡ የሰውነትዎ ቆዳ በባሕርዩ ደረቅ ከኾነ ፊት ላይ ከተቀቡ በኋላ ተልጠው የሚነሡ የፊት ማስኮችን መጠቀም የለብዎትም፡፡ ማስኩን ለማስወገድ የሚያደርጉት ጥረት የፊትዎን ቆዳ በኃይል ሊጎዳው ይችላል፡፡
በአጭር ጊዜ ደረቅ የሰውነት ቆዳን ማከም ከፈለጉ ደግሞ የዕለት ሥራዎትን ካጠናቀቁ በኋላ ሰውነትዎን በስሱ ቫዝሊን ይቀቡት፡፡ ለውጡን በጥቂት ቀናት ውስጥ ያዩታል፡፡
4. በወረቀት መልክ የሚዘጋጁ የፊት ማስኮች
እንዲኽ ዓይነቶቹ የፊት ማስኮች ብዙ ተቀባይነት ያላቸው መኾናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ምክንያቱም ውጤታማ እና ለቆዳ ተስማሚ የኾኑ ምግቦችን በፍጥነት ለቆዳ ሕዋሳት የሚያስተላልፉ በመኾናቸው ነው፡፡ በወረቀት መልክ የሚዘጋጁ የፊት ማስኮችን ከተጠቀምን በኋላ እንደቫዝሊን ያሉና የሰውነትን እርጥበት መጠበቅ የሚችሉ ማለስለሻዎችን መጠቀም ብልኅነት ነው፡፡
የትኛውንም ዓይነት የፊት ማስክ እንደምርጫዎ ሊጠቀሙ እና የሰውነትዎን ቆዳ ሊያፍታቱ እንዲኹም ሊንከባከቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሰውነትዎ ቆዳ ምንም ያኽል ዘና የማለትና የመለስለስ ስሜት እንዲሰማዎ ቢያደርግዎም ማለስለሻ ቅባቶችን ከመጠቀም እንዳይዘናጉ!
በቅርብ ጊዜ የተሰጡ አስተያየቶች
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by libe
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by alemugetahun
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by Risky
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by belay
06 Jan 2015 @ 12:35 pm by መቅደላዊት ታከለ