በቀን ምን ያህል ውሃ መጠጣት ይኖርብዎታል?
ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ውሃ ለቆዳ ጥራት፣ በሰውነት ውስጥ ያሉ መርዛማ ነገሮችን አጥቦ ለማውጣትና ለመሳሰሉት ነገሮች ያለው ጠቀሜታ ተጋኖ ይነገራል እንጅ ከመጠን ያለፈ ውሃ መጠጣት እንዲያውም ለጤና ጠንቅ ሊሆን ይችላል፡፡
ለመሆኑ የዓለማችን እጅግ ጠቃሚ መጠጥ ከሆነው ውሃ ጋር ተያይዘው የሚነገሩት እንደ ዝቅተኛ ካሎሪ፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የጡንቻ ጥንካሬና የአካል ክፍሎች ጤንነት ያሉ ጠቄሜታዎች እውነት ናቸው? በትክክል እነዚህ ሁሉ እውነት ናቸው፤ ሆኖም እዚህ ጋር ቁልፉ ጥያቄው የሚጠጡት ውሃ በቂ ነው ወይስ ከበቂ በላይ የሚለው ነው፡፡ ከበቂ በላይ ውሃ እየጠጡ ከሆነ ለሚከተሉት አደገኛ ሁኔታዎች ይጋለጣሉ፡፡
በውሃ የመመረዝ ችግር
ምናልባት ሰውነትዎ ውሃ በዛበት ሲባሉ ሊገርምዎት ይችላል፡፡ ይህ ችግር ሃይፖናትሬሚያ የሚባል ሲሆን በአደገኛ ሁኔታ በደም ውስጥ ያለው የጨው መጠን ዝቅተኛ ሲሆን የሚፈጠር ችግር ነው፡፡ ይህም ኩላሊትዎ ሊያጣራው ከሚችለው በላይ ውሃ ሲጠጡ የሚከሰት ነው፡፡
ከመጠን በላይ ማላብ
ከመጠን በላይ ውሃ መጠጣት ሃይፐርሃይድሮሲስ ወይም ብዙ ላብ ማላብን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይሄ ታዲያ ጤነኛው የማላብ አይነት አይደለም፤ በፍፁም! ሊጠነቀቁበት የሚገባውን የሚንጠባጠብ፣ በሰውነትዎ ላይ የሚወርደውን አይነት ላብ ለማለት ነው፡፡
ኢንሶሚኒያ (እንቅልፍ ማጣት)
ከመተኛታችን በፊት ሰውነታችን የኩላሊትን ስራ ዝግ የሚያደርግና እንቅልፍ ላይ ሆነን ሽንታችን እንዳይመጣ የሚያደርግ ኤ.ዲ.ኤች. (አንቲዲዩሬቲክ ሆርሞን) የተባለ ሆርሞን ይረጫል፡፡ ከመኝታ በፊት በጣም ብዙ ውሃ መጠጣት ይሄንን ሆርሞን ስራውን እንዳይሰራ ያደርጋል፤ ስለዚህ በምሽት ብዙ ውሃ ባለመጠጣት እንቅልፍ የሚነሳዎትንና ለንጭንጭ የሚዳርግዎትን በሌሊት ለሽንት የመነሳት ችግር ያስወግዱት፡፡
ምን ያህል ይበቃል?
በቀን መጠጣት ያለበት ትክክለኛ የውሃ መጠን ሁለት ሊትር ነው፡፡ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት (The National Health Service (NHS)) የተሰኘው የእንግሊዝ ድርጅት ደግሞ በቀን 1.6 ሊትር ውሃ ብቻ እንድንጠጣ ይመክራል፡፡ ሲንጋፖር ውስጥ ያለው የራፍልስ ሆሰፒታል የእጢ በሽታዎች ስፔሻሊስት የሆኑት ስታንሊ ሊው እንደሚሉት “በቀን በአማካይ 1.6 ሊትር ወይም ስድስት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት በቂ ነው፡፡” በርሃ ላይ ካልሆኑ ወይም ንፁህ ውሃ ማግኘት ካልቻሉ በስተቀር በሰዓት ከ1.5 ሊትር በላይ ውሃ መጠጣት ጤናማ ነገር አይደለም፡፡
ከመጠን ያለፈ ውሃ መጠጣትዎን በምን ያውቃሉ? ሽንትዎን ሲሸኑ መልኩን ያጢኑት፡፡ ያልደመቀ ወይም ፈዛዛ ቢጫ መሆን አለበት፡፡ ደማቅ ቢጫ ከሆነ ተጨማሪ ውሃ መጠጣት እንዳለብዎት አመላካች ነው፡፡ በጣም ፍዝ ወይም ከሞላ ጎደል ጥርት ያለ መልክ ያለው ከሆነ ደግሞ ከመጠን በላይ ውሃ መጠጣትዎን ያሳያል፡፡
በቅርብ ጊዜ የተሰጡ አስተያየቶች
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by libe
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by alemugetahun
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by Risky
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by belay
06 Jan 2015 @ 12:35 pm by መቅደላዊት ታከለ