ቆዳዎን ፀሃይ ከምታስከትለው የቆዳ መጥቆር ችግር ይታደጉት
በብዙዎች ዘንድ አንዳንድ የሎሽን ምርቶች ለቆዳ መጥቆር ችግር ይዳርጋሉ የሚል የተሳሳተ እምነት አለ፡፡ እውነቱ ግን እነዚህ ሰዎች የችግሩን ትክክለኛ ምንጭ በአግባቡ አለመረዳት ነው፡፡ ቆዳዎን የሚያጠቁረው ሎሽን ሳይሆን ፀሐይ ናት፡፡ የፀሐይ ብርሃን በቆዳችን ውስጥ ያለውን የቀለም ክምችት መጠን ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የፀሐይ መከላከያ ሲጠቀሙ ቆዳዎ ርጥበት እንዲኖረው እና ደህንነቱ እንዲጠበቅ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከመጥቆር ችግርም ጠበቁት ማለት ነው፡፡
በተጨማሪም የተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች የሚያስፈልጋቸው የእንክብካቤ አይነት እንደዚሁ የተለያየ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይህም የሚሆንበት ምክንያት ፀሐይ በሁሉም የሰውነታችንን ክፍሎች ላይ የሚኖራት ተፅዕኖ አንድ አይነት ስላልሆነ ነው፡፡ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችዎን ለመንከባከብ፣ ጤንነታቸውን እና የእርጥበት ልካቸውን ለመጠበቅ እንዲሁም ቆዳን ለጥቁረት ከሚዳርጉ ጎጂ የፀሐይ ጨረሮች ለመጠበቅ ከዚህ በታች የቀረቡትን ጠቃሚ መንገዶች ልብ ይበሏቸው፡፡
1) ክርን
ክርንዎ እጅግ በጣም ከሚጠቀሟቸው እና ተጋላጭ ከሆኑ የሰውነትዎ ክፍሎች የሚመደብ ነው፡፡ ክርንዎ ይታጠፋል፤ ይዘረጋል፤ እንዲሁም ቀኑን ሙሉ ሲደገፉበት ይውላሉ፡፡ ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ቆዳን ቀለሙን ለሚያሳጡ እና ጉዳት ለሚያስከትሉ የድርቀት እና የመደንደን ችግሮች ያጋልጣል፡፡ ከዚህ ጉዳት ለማገገም በመጀመሪያ ቆዳዎን በቀላሉ በመታጠብ፣ ከዚያም በስኳር በመፈግፈግ በመጨረሻም በሰውነት እንክብካቤ ልማድ መሰረት አስፈላጊውን ርጥበት እንዲያገኝ ያድርጉት፡፡
2) እግርዎ
የእግርዎ ቆዳ በተፈጥሮው ከየትኛውም የሰውነት ክፍል ቆዳ ይልቅ ደረቅ ነው፡፡ ቅባት የሚያመነጩ ዕጢዎች ስለሌሉት ቆዳ የሚፈልገውን ርጥበት ለመስጠት የሚጠቀመው የላብ አመንጪ ዕጢዎችን ነው፡፡ ባዶ እግር በሚረግጣቸው የተለያዩ ወለሎች የተነሳ ተጋላጭነቱ ከፍተኛ በመሆኑ የእግርዎን ቆዳ እርጥበት መጠበቅ እና ከጉዳት መከላከል ያስፈልጋል፡፡
3) እጅዎ
እጆቻችን ሁልጊዜም ለጉዳት የተጋለጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ የየዕለት ሥራችንን ለመሥራት አብዝተን እንጠቀምባቸዋለን፡፡ የእጃችን ቆዳ በጣም የሳሳ ነው፡፡ ከፊታችን ቆዳ በላይ የእጃችን ቆዳ ይሳሳል፡፡ በተጨማሪም የዕድሜ መጨመርን በተመለከተ ምልክት ከሚያሳዩን የሰውነት ቆዳዎች ውስጥ የእጅ ቆዳ አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ደረቅ አካባቢ የሚያደርገው አስተዋፅኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እጅን በተደጋጋሚ መታጠብም (በተለይ በሞቀ ውሃ) ቆዳ ራሱን ለመከላከል የሚጠቀምበትን የላይኛውን ክፍል ይጎዳዋል፣ ርጥበቱን ጠብቆ የመቆየት አቅሙንም ያዳክመዋል፡፡
4) ጉልበትዎ
እንደክርንዎ ሁሉ ጉልበትዎም በቋሚነት የሚታጠፍ እና ብዙውን ጊዜ ለአየር ተፅዕኖ (እንደ ወቅቱ ሁኔታ) የተጋለጠ ነው፡፡ የጉልበትዎ ቆዳ ጠንካራ ነው፡፡ ሆኖም ልክ እንደክርንዎ ጉልበትዎም ለተመሳሳይ ድርቀት፣ ጉዳት እና የተፈጥሮ ቀለም ማጣት ችግሮች ተጋላጭ ነው፡፡ የጉልበትዎን ርጥበት በአግባቡ መጠበቅዎን ያረጋግጡ፡፡
ስለቆዳ ጤንነት ስንነጋገር፣ ፊታችን እና እጃችንን ለመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎቻችን ብቻ ማዳላት የሚባል አደገኛ ጨዋታ መጫወት እንደሌለብን ልብ ልንል ይገባል፡፡ መላ አካላችንን ለመንከባከብ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡
በቅርብ ጊዜ የተሰጡ አስተያየቶች
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by libe
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by alemugetahun
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by Risky
06 Jan 2015 @ 12:28 pm by belay
06 Jan 2015 @ 12:35 pm by መቅደላዊት ታከለ